top of page

ግልፅ ደብዳቤ - ለጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ

  • hannaalemu08
  • Jan 9, 2022
  • 3 min read

ግልፅ ደብዳቤ - ለጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ - የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር

የአሸባሪው ሕወሃት መሪዎችን በምህረት ስለመለቀቅ በሚመለከት

01/09/22


ክቡር ጠ/ሚር

በሀገራች ሰላም እንዳይሰፍን ውስጣዊ እና ውጫዊ ጠላቶቻችንን የሀገራችንን ሰላም ለማጠልሸት አልፎ ተርፎም የዜጎችን የእለት ከእለት ኑሮ ለማደናቀፍና በአጠቃላይ የሀገራችንን ህዝብ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለመክተት ባደረጉት ሴራ የተነሳ በርካታ ዜጎች የህይወት ማጣትን ጨምሮ አካል መጉደልና ከአካባቢያቸው ቤት ንብረታቸው እየወደመ ተሰደዋል፤ ይሁንና ከውስጥ የአሸባሪው የህወሀት እና የደጋፊዎቹ ሴራ ከውጭ ደግሞ በርካታ ሀያላን የምእራባዊያን ጣልቃ ገብነት ተጨምሮ ሀገራችን እና ህዝባችን ወደ አልፈለገው የህልውና ጦርነት ውስጥ በመግባት “ኢትዮጵያን እንበትናለን” ብለው የተነሱትን ሀይሎች ከፍተኛ የህይወት መስዋእትነት በመክፈል አሸባሪውን የህወሃት ሀይል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አስወግደናል። ጦርነቱንም በአጠረ ግዜ አለመጨረሳችን የሚያስከትለብን ፈተና ከባድ እንደሆነ በሚገባ ታዝበናል፤ የተራዘመ ጦርነት እንደ እሳት ነበልባል ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይበላል፤ ለውጭ ጠላቶቻችንን የበረታ ጫና ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቱም እጅግ የበዛ ነው፡፡ ይሄንን አስከፊ ጦርነት በአጭር መስዋእትነት ለማጠቃለል፤ እንዲሁም አሁን በቅርቡ የሚጀመረውን አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ለማድረግ መንግስት ለተሻለ ፖለቲካዊ ምህዳር ለማምጣት በሚል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት በምሕረት ከእሥር ፈትቷል። በእርግጥ ነው ምህረት አገራዊ መግባባትን እንደሚፈጥር እና የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልህና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ እንደሚፈታ በጽኑ እንገነዘባለን፤ አልፎ ተርፎም የሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታች መሆኑን በሚገባ እንደግፋለን፤ ይሁንና መረሳት የሌለበት ጉዳይ ግን በዘረኛው እና አሸባሪው የህወሃት ቡድን ላለፉት ፴ አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍና በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፤ በተለይ በዚህ አንድ አመት ውስጥ የወያኔ አሸባሪ ሃይል በሰሜኑ ግንባር የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ በካሃዲነት ያደረሰው ጥቃት እንዲሁም በአማራና አፋር ተወላጆች ላይ የፈጸመው እጅግ ዘግናኝ አረመኒያዊ ጭፍጨፋ ቀላል እንዳልነበር ይታወቃል።

አሁንም ሀገራችንን ለመገነጣጠልና የተለያዩ ዘር ተኮር የእርስ በርስ እልቂት ለማምጣት የሚያደርገውን ሙከራ አጠናክሮ እየቀጠለ እንዳለ የሚታወቅ ነው፤ በሌላ በኩል ህብረተሰባችን ገና ከደረሰበት ግፍና የሀዘን ስሜት ያላገገመ ቢሆንም እንደ ማህበረሰብ በውጭም በውስጥም ያለውን ኢትዮጵያዊ ተባብሮ በጋራ ጠላቶቻችንን ለመቋቋም ከፍተኛ ተጋድሎ እያረገ ባለበት ባሁኑ ወቅት በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊም ለሀገርና ለወገን ያለውን ድጋፍ ለማሳየት እንዲሁም አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀያላን የምእራባዊያን መንግስታት ሲያደርጉት የነበረውን ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማ ለመቃወም በአንድነት በመቆም ሲያደርጋቸው የነበሩ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲሁም በጦርነቱ የተነሳ የተጎዱቱን ወገኖቹን ለመርዳት ከልጆቹ ጉሮሮ እየነጠቀ የህዝብ እና የሀገር ጉዳይ ይበልጥብኛል በማለት የተቻለውን ሁሉ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡ በዚህ ላይ በቅርቡ እርሶ ያቀረቡትን ሀገራዊ ጥሪ አስመልክቶ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ህዝባችንን እና ሰራዊታችንን በተቻላቸው መጠን ለመደጎም እንዲሁም በሞራል ለማጽናናትና ፍቅራቸውን ለማሳየት ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሀገር ቤት በመግባት ላይ እንዳሉ ይታወቃል።

እንደሚታወቀው አለማጋነን በእኛ የህይወት ዘመን ለመጀመሪያ ግዜ በሀገር ቤትም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊያን እና ትውለደ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም በእርስዎ የሚመራውን መንግስት በገንዘብ፣ በሞራል፣ በጉልበት፤ በእውቀትና በአጠቃላይ ግዜውን ሁሉ መስዋእት በማድረግ በየትኛውም ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፤ ነገር ግን ይሄንን በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን እና በሌሎች የክልል ሚሊሺያና ልዩ ሃይሎች እንዲሁም በፋኖና ደጀን በሆነው በውስጥም በውጭም ባለው ወገናችን በተከፈለ ከፍተኛ መስዋእትነት እየተገኘ ያለን ድልና የአንድነት መንፈስ በሚያናጋ መልኩ የተደረገው የዚህ ሁሉ ወንጀል ቀንደኛ ተጠያቂና የጥፋት ቡድኑ መሪዎች የሆኑትን ወንጀለኞች በምህረት ስም ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ በየግንባሩ ለአገር ሉአላዊነት እና ለአንድነታችን በሚል ሲሞት እና ሲቆስል የነበረውን የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን፣ በደል የደረሰባቸውን ወገኖቻችን እና በአጠቃላይ የመላው ሀገር ወዳድ ወገኖቻችንን ልብ የሚሰብር ሁኔታ መፈጠሩ እኛንም ያሳዘነን ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በእርሶ እና በመንግስት የተገቡ የህግ የበላይነትና የፍትህ ስርአትን የማክበር ቃሎች እንዲከበሩና ያለአግባብ ከእስር የተለቀቁት የወያኔ አሸባሪ አመራሮች ውሳኔ ለሕዝብና ለሀገር አንድነት ሲባል ውሳኔውን በመቀየር በእስር ቆይተው የህግ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ እንዲደረግ በደል በደረሰበት ወገናችን ስም በማክበር እንጠይቃለን። ለወደፊቱም መንግስት የዚህን አይነት የህዝብና የአገር አንድነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ ውሳኔዎችን ከመውሰዱ በፊት ህዝብን ያማከለ በቂ ምክንያትና ማብራሪያ ቢሰጥ ህዝብን ከውዥብር ለመታደግና እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሀገር እና ህዝብ እንዳይረጋጋ የሚዳክሩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጠላቶችን ማምከን ይችላል።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሽንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል


Comments


Negere-Amhara is a space dedicated to keeping this website's visitors informed on historical and current developments surrounding the people of Amhara. 

  • White Facebook Icon
bottom of page